በአርባምንጭ ከተማ ኢ ዲ አይ ኢትዮጵያ የአለም አቀፍ የሥራ ፈጣሪዎች ሳምንት "ሥራ ፈጣሪነት ለሁሉም" በሚል መሪ ቃል ተከበረ።

አርባምንጭ:- ህዳር 14/2017 ዓ፣ም(አርባምንጭ ከተማ መንግስት ኮሙኒኬሽን) 

በመርሃግብሩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ም/ርዕስ መስተዳድርና የክልሉ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገ/መስቀል ጫላ ኢ ዲ አይ ኢትዮጵያ ከተመሰረተ እንደሀገር ያለውን የስራ ፈጠራ አስተሳሰብ ክፍተቶችን በመሸፈንና የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ የተሰሩ በርካታ ስራዎችን የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የኢ ዲ አይ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሀሰን ሁሴን በበኩላቸው ኢ ዲ አይ ኢትዮጵያ እንደሀገር ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም በመፍጠር ሀገርን ለመገንባት ውጤታማ፣ ደፋር ችግር ፈቺ ዜጋ በማፍራት ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ለማስቻል እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የኢ ዲ አይ ኢትዮጵያ የሪጅናል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ጌትነት ሳሙኤል አክለውም በ2017 ዓ፣ም 832 ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረው በዛሬው ዕለትም በሶስት ዘርፎች ማለትም 16 EMPRTEC trainers፣ 28 BOA trainers እና 24 EBMS trainers በድምሩ 68 ስልጠና የወሰዱ ሰልጣኞች መመረቃቸውን ገልፀዋል።

የኢ ዲ አይ ኢትዮጵያ አርባምንጭ ከተማ አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሪት ሙሉወርቅ በቀለ አክለውም እስካሁን በቤሬ እና ነጭ ሳር አንድ የEDI-WEDP መመዝገቢያ ቦታዎች 750 ሴት ስራ ፈጣሪዎች ተመዝግበው 460 ስልጠናውን መውሰዳቸውን ገልፀው በተጭማሪ በኢ ዲ አይ ኢትዮጵያ በኩል ስልጠና ከወሰዱ ኢንተርፕራይዞች ለ66 ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር አገልግሎት ተመቻችቶላቸው ሂደት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በመርሃግብሩ በስራ ፈጠራ ውጤታማ የሆኑ ኢንተርፕራይዞች ተሞክሮዎቻቸውን ያጋሩ ሲሆን ባለድርሻ አካላትም ለስራ ፈጣሪዎች የክህሎት መር ስልጠናዎችና አቅጣጫዎችን በመጠቀም፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ የቦታና ብድር አቅርቦት በማመቻቸት እንዲሁም ድጋፍና ክትትል በማድረግ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በመወጣት የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቁሟል።