የንግድ ፈጠራ ስራ ባለቤቶችን የማጠናከርና የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል:- የስራና ክህሎት ሚኒስቴር



የንግድ ፈጠራ ስራ ባለቤቶችን የማጠናከርና የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ። ዓለም አቀፍ የንግድ ስራ ፈጣሪዎች (ኢንተርፕርነርሺፕ) ሳምንት "ኢንተርፕርነርሺፕ ለሁሉም" በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ሲካሔድ ቆይቷል። የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንቱ በዓለም ለ16ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ10ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ አካላት በቀጥታ እና በበየነ መረብ ተሳትፈዋል። የፓናል ውይይቶች፣ አውደርዕዮች፣ ኮንፈረንሶች፣ ሴሚናሮች፣ የእርስ በእርስ ትውውቅና የልምድ ልውውጦች የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንቱ አካል ነበሩ። የበዓሉ የመዝጊያ ፕሮግራም የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በተገኙበት ትናንት ማምሻውን ተከናውኗል።

በመድረኩ በተለያዩ የስራ ፈጠራ ዘርፎች ተወዳድረው ብልጫ ያስመዘገቡ የአመቱ ምርጥ ስራ ፈጣሪዎች ከስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እውቅና ተበርክቶላቸዋል። ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በምታደርገው ርብርብ የኢንተርፕርነሮች ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል። በርካታ የዓለም ሀገራት ችግሮችን ተሻግረው ከሐብት ማማ የደረሱት ለስራ ፈጠራ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ከለውጡ ወዲህ መንግስት ለስራ ፈጠራ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱንና በዚህም አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል። ዜጎች ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበትና የፋይናንስ ክፍተቶቻቸውን የሚሞሉበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ነው ያስረዱት። አሁን ላይ በርካታ ዜጎች ከስራ ጠባቂነት ወደ ስራ ፈጣሪነት በመሸጋገር ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች አማራጭ የስራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን አመላክተዋል።

በቀጣይም የንግድ ፈጠራ ስራ ባለቤቶችን የማጠናከርና የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። የኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሐሰን ሁሴን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሰዎች ክህሎታቸውን አውጥተው ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ስልጠና መስጠት ከኢንስቲትዩቱ ተልዕኮዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ የዜጎችን የክህሎት ክፍተት ለመሙላት አሁን ላይ በመላው አገሪቱ 5 ሺህ 600 አሰልጣኞች መመደቡን ገልጸዋል። በዚህ በ2017 በጀት አመት የመጀመሪያው ሩብ አመት ብቻ 500 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠና መስጠቱን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

https://www.facebook.com/100068925410833/posts/pfbid0vaVgMfT5R7CFm9hfL19SNZCxnCSJ6GCXK8PL65gq55nTiah65mzr9iULJfXoAEc7l/

https://www.youtube.com/watch?v=KEknlncjuVE